አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት እስካሁን በተለያየ ምክንያት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ያልተሳተፉ አካላት እንዲሳተፉ ለማድረግ ይሰራል አለ።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በተጠናቀቀው 2017 የተከናወኑ ተግባራት እና በ2018 ዓ.ም የሚሰሩ ስራዎችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው ዓመት ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች አጀንዳ መሰባሰቡን አስታውሰው፤ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ የሚሳተፋ ተወካዮችን መምረጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑን እንቅስቃሴዎች ግልፅና ተደራሽ ማድረግ፣ በምክክር ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠርና አጋርነቶች እንዲጠናከሩ ተሰርቷል ነው ያሉት።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የምክክር አስፈላጊነት እና የኮሚሽኑ ገለልተኝነትና ነፃነትን ላይ የተሻለ አረዳድ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ከዳያስፖራው ጋር እየተደረጉ የሚገኙት የምክክር መድረኮች ውጤት እየታየባቸው ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የዳያስፖራው አጀንዳ ማሰባሰብና ተወካዮች መረጣ ይከናወናል ብለዋል።
የትግራይ ክልል በምክክር ሂደቱ እንዲካተት ለማድረግ እንደሚሰራ፣ በምክክር ሂደቱ ያልተሳተፉ እና ሲሳተፋ ቆይተው ያቋረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በትጥቅ ትግል ያሉ ኃይሎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ይሰራል ነው ያሉት።
አጀንዳ በመቅረጽ ምክክር የሚደረግባቸውን እና ሌሎች አጀንዳዎች ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁመው፤ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ምክክሩ ተካሂዶ መግባባት ላይ እንዲደረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንሚቀጠል አስረድተዋል፡፡
በቅድስት አባተ