Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ መተግበር የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ መተግበር በአሰራር ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ገለጸ።

በአገር አቀፍ ደረጃ የ10 ዓመት ብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ሲዘጋጅ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ከባለፈው አመት ጀምሮ እየተተገበረ ያለው ስትራቴጂ በተለይ በሎጅስቲክስ ስርአቱ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በሎጀስቲክስ ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶች ከአገሪቱ የገቢና ወጪ እድገት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን ገልጸው እቃዎችን በፍጥነት በማስገባትና በማስወጣት ረገድም ውስብስብና አመቺ ያልሆኑ አሰራሮች እንደነበሩ ያነሳሉ።

በዚህም እቃዎችን በማጓጓዝ ሂደት ላይ ቀልጣፋ አሰራር ባለመኖሩ የሚፈልገው ወጪም ከፍተኛ መሆኑን ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገር ውሰጥ የሚገቡና የሚወጡ የወደብ እቃዎች እየጨመሩ ቢሆንም የወደብ የማስተናገድ አቅም ግን ውስን መሆኑን አቶ መኮንን ይገልፃሉ።

ከመርከብ የሚራገፉ እቃዎችን በአፋጣኝ ለማንሳት የአቅም ውስንነት መኖርም ሌላኛው ችግር መሆኑን ይናገራሉ።

አሁን ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት፣ ባቡርና መኪና እያደገ ከመጣው የገቢና ወጪ የወደብ እቃዎች ጋር ሲነፃፀር የሚመጣጠን አለመሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የሎጅስቲክ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአገሪቱ በኮንቴነር ታሽጎ ወደ ውጭ የሚላክ እቃ 7 በመቶ የነበረ ሲሆን ባለፈው አመት እና በያዝነው አመት ግን 52 በመቶ እቃ በአገር ውስጥ በማሸግ መላክ ተችሏል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ ደግሞ ይበልጥ ውጤታማ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የብሄራዊ የሎጅስቲስ ካውንስል እንዲሁም የሎጅስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ የተቋቋመ ሲሆን ይህም ለዘርፉ እድገትና ውጤታማነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version