Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተጠባቂ ጨዋታዎች ተመልሷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ሳምንታት እረፍት በኋላ የማንቼስተር ደርቢን ጨምሮ በተጠባቂ የ4ኛ ሳምንት መርሐ ግብሮች ይመለሳል፡፡

በ2026 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ መርሐ ግብር ለየሀገራቸው ሲጫወቱ የሰነበቱ ተጫዋቾች ወደ ክለቦቻቸው ተመልሰዋል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ የ4ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገ ቀን 8፡30 አርሰናል በኢምሬትስ ስታዲየም ኖቲንግሃም ፎረስትን በሚያስተናግድበት የምሳ ሰዓት ጨዋታ ጅማሮውን ያደርጋል፡፡

ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፈው በሊቨርፑል ሽንፈት ያስተናገዱት መድፈኞቹ በ6 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፥ ለነገው ጨዋታ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡

አሰልጣኝ ኑኖ እስፒሪቶ ሳንቶን ተክተው ፎረስቶችን የተረከቡት የቀድሞው የቶተንሃም ሆትስፐር አሰልጣኝ አንጄ ፖስቴኮግሉ አዲሱ ክለባቸውን እየመሩ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ቦርንማውዝ ከብራይተን፣ ክሪስታል ፓላስ ከሰንደርላንድ፣ ኤቨርተን ከአስቶን ቪላ፣ ፉልሃም ከሊድስ እንዲሁም ኒውካስል ከወልቭስ ነገ 11 ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

በዕለቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር ነገ ምሽት 4 ሰዓት ቼልሲ ከሜዳው ውጭ ብሬንትፎርድን የሚገጥም ሲሆን፥ ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ምሽት 1፡30 በለንደን ደርቢ ዌስትሃም ከቶተንሃም ይገናኛሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ እሑድ ቀጥሎ ሲደረግ፥ በሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር ምሽት 12፡30 ኢቲሃድ ስታዲየም የማንቼስተር ደርቢን ያስተናግዳል፡፡

ሊጉን በድል ከጀመሩ በኋላ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ማንቼስተር ሲቲዎች ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀላል ይሆንላቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ከከተማ ተቀናቃኛቸው ማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ አስቀድሞ በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ማጣታቸው ለፔፕ ጋርዲዮላ ሌላ ፈተና መሆኑ ተነግሯል፡፡

ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂያቸውን አንድሬ ኦናና በውሰት ለቱርኩ ክለብ ትራብዞንስፖር አሳልፈው የሰጡት ዩናይትዶች በሊጉ 2ኛ ድላቸውን ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በኢቲሃድ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ባለሜዳዎቹ ሲቲዎች ሦስቱን ሲያሸንፉ ማንቼስተር ዩናይትድ በሁለቱ ድል ቀንቶታል፡፡

ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 10 ሰዓት ላይ በሊጉ በብቸኝነት ሦስቱንም የመጀመሪያ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሊቨርፑል ከሜዳው ውጭ በርንሌይን ይገጥማል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version