አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል አርብቶ አደሮች በግብርና ሥራ በስፋት እንዲሰማሩ የተጀመረው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው አለ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ፡፡
የቢሮው ሃላፊ አቶ መሐመድ አሊ ቢኢዶ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ከለውጡ በፊት በአፋር ክልል የግብርና ሥራ ውጤታማ አያደርግም የሚል ነጠላ ትርክት ነበር፡፡
የለውጡ መንግስት ግን መሰል ነጠላ ትርክቶችን በመቀየር አርብቶ አደሮች በግብርና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠትና የግብዓት አቅርቦት በማሟላት ለዘመናት ሳይለሙ የቆዩ መሬቶችን ማልማት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይም በክልሉ ሁሉም ዞኖች የመልማት አቅም ያላቸውን የእርሻ ቦታዎች በመለየት በዘር መሸፈን መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በተከናወነው ሥራ በክልሉ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የሙዝ፣ የፓፓያ፣ ብርቱካን ሌሎች የፍራፍሬ ምርቶች መመረታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ አርብቶ አደሮች ለዘመናት ያሳለፉትን የአኗኗር እና የሕይወት ዘዬ በመቀየር በአርሶ አደርነት ሙያ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ይህን ተከትሎም አርብቶ አደሮች ከተረጂነት በመውጣት በራሳቸው አቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡
የክልሉ መንግስትም በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ተገቢ የክትትል ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በአካል በመገኘት የአርብቶ አደሮችን የእርሻ ሥራ ማበረታታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ አፋር ክልልን የግብርና ማዕከል በማድረግ የተጀመረውን የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ሥራ እውን ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ