Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጽንፈኛው ፋኖ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል በውክልና ጦርነት ሀገር ለማፍረስ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛው ፋኖ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል በውክልና ጦርነት ሀገር ለማፍረስ እየሰራ ነው አለ እጁን ለመንግስት የሰጠው የቡድኑ የመረጃና ደህንነት ሃላፊ ያረጋል አያና ።

በአማራ ክልል ራሱን “የራስ መንገሻ አቲከም ክፍለ ጦር” ብሎ የሚጠራው ጸንፈኛ ቡድን የመረጃና ደህንነት ሃላፊ የነበረው ያረጋል አያና መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል እጁን ለመንግስት ሰጥቷል።

የጽንፈኛ ቡድኑ መሪዎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልእኮ ተቀብለው ለማስፈጸም እንደሚሰሩም አጋልጧል።

የጽንፈኛ ቡድኑ ከፍተኛ አመራር የነበረው ያረጋል አያና÷ በተሳሳተ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ተደናግሮ ጽንፈኛ ቡድንን መቀላቀሉንና ከአባልነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ደረጃ ድረስ መስራቱን ተናግሯል።

ጽንፈኛ ቡድኑ በአንደበቱ ለሕዝብ እንደሚታገል ቢገልጽም በተግባር ግን የአማራ እናቶች የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ፤ ልጆቻቸውን እንዳያስተምሩ እያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡

አርሶ አደሩ ለዘር ያስቀመጠውን እህል እና ለማዳበሪያ የቆጠበውን ገንዘብ ሳይቅር በመንጠቅ ጸረ ሕዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያለው።

የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳን በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው እንዲሸጡ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ የሚሰበሰብ ገንዘብን በመንጠቅ ከፍተኛ አረመኔያዊ ተግባር እንደሚፈጽምም አጋልጧል።

ጽንፈኛ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ህብረት በመፍጠር ሀገር ለማፍረስ የውክልና ጦርነት እያካሄደ መሆኑን ገልጾ÷ ይህም እጅግ አስነዋሪ ተግባር በመሆኑ የመንግስትን የሰላም ጥሪ መቀበሉን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ አስፈጻሚ የሆኑት የቡድኑ አመራሮችም÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በድል በመጠናቀቁ እጅግ ማዘናቸውንም ነው የገለጸው።
በተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎች ተደናግረው ጽንፈኛ ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶች የቡድኑን መሰሪ አካሄድ እየተገነዘቡ መሆኑንም ገልጿል።

እነዚህ ወጣቶች ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱላቸው የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

ጽንፈኛ ቡድኑ አሁን ላይ እጅግ ተስፋ እየቆረጠ መሆኑን ጠቅሶ፤ ማህበረሰቡ የቡድኑን አፍራሽ ተልዕኮ በመረዳት ከመንግስት ጎን ሆኖ እየታገላቸው እንደሆነ መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሁሉም የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version