Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ድንቅ መሰረት ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታሪካችን እውነተኛ እጥፋትና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ድንቅ መሰረት አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ግድቡ ተጠናቅቆ ለምረቃ መብቃቱን በማስመልከት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመዲናዋ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ግድቡ ለኢትዮጵያ የብሩህ ተስፋ ቀንዲል፣ የታሪካችን እውነተኛ እጥፋትና የማንሰራራት ድንቅ መሰረት የሆነ ታሪካዊ ድል መሆኑን አውስተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ድልና የእንጉርጉሯችን ማብቂያ ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ በግድቡ ግንባታ ሂደት በየዘርፉ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቁጭትና ሀሳብ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር ቆይቶ ለፍጻሜ መብቃቱን ገልጸው፥ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆርጠን ስንነሳ የትኛውም ተፅዕኖ አያስቆመንም ነው ያሉት፡፡

ሳይሰስቱ ሁሉ ነገራቸውን ለኢትዮጵያ የሰጡ፣ በጉባ ተራራ ፈታኝ በሆነው ቦታ ለሀገራቸው የቆሙና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነታችን የተሟገቱትን ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናቸዋለች ብለዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆርጠን ስንነሳ የትኛውም ተፅዕኖ ሊያስቆመን አይችልም ያሉት ከንቲባዋ፥ በራሳችን ገንዘብ፣ ላብ እና የደም ዋጋ ግድቡ ተጠናቅቆ ለምረቃ መብቃቱን አንስተዋል፡፡

የእኛ ትውልድ ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪ መሆኑን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሳይቷል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ግድቡ በራስ አቅም የመልማት፣ የቁርጠኝነትና የዚህ ትውልድ ውጤት መሆኑን ጠቁመው፥ የኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት ምላሽ ነው ብለዋል፡፡

Exit mobile version