Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የዓባይ ወንዝ ውሃ ባለድርሻ እና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የዓባይ ወንዝ ውሃ ባለድርሻ እና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ በባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በድጋፉ ሰልፍ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ኢትዮጵያ የልማት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተሰጣትን ሀብት በራሷ አቅም፣ በራሷ ሀብት፣ ፈተናዎችን ተቋቁማ፣ ለአፍሪካ ምሳሌ በሚሆን መልኩ አጠናቅቃለች ነው ያሉት።

ሕዳሴ ግድቡ አባቶች እንዳሳኩት የዓድዋ ድል ሁሉ በዚህ ዘመን የተሳካ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠላቶች የጠነሰሱትን ጥሰን እና በጣጥሰን በአንድነት ቆመናል፤ ዛሬም በፍጹም አርበኝነት አሸንፍናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጫናውን ተቋቁማ፣ የሕዝቦቿን አንድነት እና አይበገሬነት ተጠቅማ ድል ማድረጓን የተናገሩት አቶ አረጋ÷ የሕዳሴ መጠናቀቅ ሉዓላዊ ሀገራት ሁሉ የራሳቸውን ሀብት ማንንም ሳይጠይቁ መጠቀም እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕዳሴ የቅኝ ግዛትን ውል እስከመርዙ የፈወሰ፣ የራሳችን ሀብት የተጠቀምንበት ሲሉም አብራርተዋል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ትልቅ አቅም ያለው እና በአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት መሆኑን መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የሚበቃ፣ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር፣ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬን የሚያመጣ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ተደማጭነቷ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ቅቡልነት ያሻሻለ፣ ከፈጣሪ የተሰጠን፣ በሕዝባችን አበርክቶ የተገኘ ክብርና እና ኩራት መሆኑንም ገልጸዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version