አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ በደሴ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
በሰልፉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እንዳሉት÷ ዓባይ ለምንጩ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷ የሆነውን የዓባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ታሪካዊ ጠላቶች ሦስት ዋና ዋና መንገዶችን በመጠቀም እንቅፋት ሲሆኑ ቆይተዋልም ነው ያሉት፡፡
አንደኛው ስልት ኢትዮጵያን ከውጪ ወራሪ ጋር በመሆን በመውጋት ማዳከም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም የእርስ በርስ ግጭትን በማስነሳት መንግስታዊ ሥርዓቱን በማዳከም በእርዳታ የምትኖር ደካማ ሀገር ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ እና እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችን እንዳትገነባ ማድረግ ሌላኘው ስልታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የጠላቶቿን ሴራ የተረዱት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመረባረብ በአፍሪካ ግዙፉን ግድብ በራስ አቅም እውን ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ ሳሙዔል÷ በቀጣይም ለተሸለ ስኬት መረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የታጠቁ ኃይሎች ኢትዮጵያ ትንሳዔዋን እውን ለማድረግ ቆርጣ መነሳቷን በመረዳት ወደ ሰላማዊ አማራጭ መመለስ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በአቤል ነዋይ