Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዓባይን ውሃ ለብቻቸው ሲጠቀሙ የነበሩ አካላት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እንዲቀጥሉ ይፈልጋሉ – ጌዲዮን አስፋው (ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓባይን ውሃ ለብቻቸው ሲጠቀሙ የነበሩ አካላት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እንዲቀጥሉ ይፈልጋሉ አሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ጌዲዮን አስፋው (ኢ/ር)።

በዓባይ ወንዝ ላይ ግብጽ እና ሱዳን በቅኝ ግዛት ወቅት የነበሩ ስምምነቶች እንዲቀጥሉ ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልጹት ጌዲዮን (ኢ/ር)÷ በወቅቱ ኢንግሊዝ፣ ግብጽ እና ሱዳን የላይኛውን ተፋሰሱ ሀገራት ያላሳተፉ ውሎች መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ላልተሳተፈችበት ውል ተገዢ እንደማትሆን በማስገንዘብ በመላው ኢትዮጵያዊያን ትብብር ሕዳሴ ግድብን በመገንባት በውሃው የመጠቀም መብት ማረጋገጧን አመልክተዋል።

በዚህም ትልቅ ትርጉም ያለውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ እና የኤሌክትሪክ ኃይልን ማመንጨት መቻሏን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ቴክኒካል አማካሪ ዘነበ ላቀው (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በጋራ ለመጠቀም እና በዘላቂነት ለማልማት ተፋሰሱን መንከባከብና ማስተዳደር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በፈረንጆቹ 1999 የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ መፈጠሩን ገልጸዋል።

የተፋሰሱ አባል ሀገራት እየመከሩ በዘላቂነት ለመጠቀምና ይህንን ሊመራ የሚችል ቋሚ ተቋም እስኪፈጠር ድረስ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ መፈጠሩን ገልጸው÷ በዚህ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት ከ1 ዓመት ከ6 ወር በፊት የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን መቋቋሙን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ሀገራቱ በጋራ እንዲለሙና እንዲያድጉ የሚያስተባብር መሆኑን ጠቁመው÷ የተፋሰሱ ሀገራት ስምምነትም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version