Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕዳሴ ግድብ ስኬትን በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም እንረባረባለን – አቶ አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ሕዝቡን በማስተባበር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ስኬት በሌሎች የሰላምና የልማት ስራዎች ላይ ለመድገም እንረባረባለን አሉ።

“በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ ሀሳብ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የድጋፍ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በአሰላ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሰልፍ ላይ የተገኙት አቶ አወሉ አብዲ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የክልሉ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት እና ስጦታ በማበርከት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

በቀጣይም የክልሉን ሕዝብ በማስተባበር በሕዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ስኬት በዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋትና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል  ለመድገም በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ወደ ሰላም የሚመጡ አካላትን ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የክልሉ መንግስት ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ ትኩረቱን ልማት ላይ እንዲያደርግ የሰላም መንገድ ያልተቀበሉ አካላት ላይ የህግ ማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የምርት አቅርቦትን ከማስፋት ጎን ለጎን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ይጠናከራል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማስፋት ስራ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አወሉ አብዲ አስታውቀዋል።

በአምስት ከተሞች የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚዳረስ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version