አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁ የአይቻልም አመለካከትን የናደ የአዲሱ ትውልድ ደማቅ አሻራ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁን አስመልክቶ ‘በኅብረት ችለናል’ በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ህብረተሰቡ አደባባይ በመውጣት ለመንግስት የልማት ስራዎች ያለውን አድናቆት እና አጋርነት በመግለጹ ምስጋና አቅርበዋል።
በምስጋና መልዕክታቸውም፤ የሕዳሴ ግድብ ስኬት በላብ እና ደም የተገኘ ስኬት ነው ብለዋል።
በግድቡ ለፍጻሜ መብቃት የተገኘው ድል ከዓድዋ ቀጥሎ የተመዘገበ የጥቁር ህዝቦች የድል ታሪክ መሆኑን ገልጸው፤ የዓድዋ ድል ታሪክን ያደሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከውስጥ እና ከውጭ የነበሩ ውስብስብ ተግዳሮቶችን አልፎ ለስኬት መብቃቱን ጠቅሰዋል።
ለዚህ ስኬት እንዲበቃ የለውጡ አመራር በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል አመራር ወሳኝ እንደነበር ገልጸው፤ ለግድቡ ፍጻሜ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ግድቡ ለዘመናት የነበረውን የአይቻልም አመለካከት እና አስተሳሰብን የናደ የትውልዱ ደማቅ አሻራ መሆኑን ገልጸው፤ ግድቡ በአፍሪካ ቀንድ የነበረውን የውሃ ትርክት የቀየረ ነው ብለዋል፡፡
ሕዳሴ ግድብ የነጻነትና ሉዓላዊነት መገለጫ ሆኖ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ እውን እየሆነ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት።
በአቤል ነዋይ