Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሐረሪ ክልል የተገነቡ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል የተገነቡ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና ማስፋፊያና ጥገና የተደረገላቸው ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

ትምህርት ቤቶቹን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዘካሪያ አብዱላዚዝ እንዳሉት፥ በዛሬው ዕለት ለምረቃ ከበቁት ትምህርት ቤቶች መካከል በድሬ ጠያራ ወረዳ አዲስ የተገነባው የሀሰን ጌይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም በአቦከር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ ሦስት ወለል ህንፃ የማስፋፍያ ስራ የተከናወነ ሲሆን፥ ለሐረር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥገና ተደርጓል፡፡

የመማሪያ ክፍሎቹ በጥራትና ፍጥነት የተገነቡና አስፈላጊው የትምህርት ግብዓት የተሟላላቸው መሆኑን ጠቁመው፥ ለግንባታ ስራው ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

ከትምህርት ቤቶቹና መማሪያ ክፍሎቹ ምረቃ በማስቀጠል የክልሉ የትምህርት ጉባኤ እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version