አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ተጨማሪ የልማት ጉልበት ያገኛል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የድጋፍና የደስታ መግለጫ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ የተካሄዱትን ሰልፎች አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በግድቡ የታየው ትዕምርታዊ ተግባር ሕዝቦችን ዋና ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረገ የላቀ የልማት አፈጻጸም ነው ብለዋል፡፡
የተፈጥሮ በረከት የበዛለትና የበርካታ ቅመማ ቅመሞች መገኛ የሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሕዳሴ መጠናቀቅ ተጨማሪ የልማት ጉልበት ያገኛል ነው ያሉት።
የድጋፍ ሰልፎቹ ትናንትን መነሻ በማድረግ እንደ ሀገር ወዳለምናቸው የኢትዮጵያ ብልጽግና መዳረሻዎች ለመድረስ የጥንካሬ መንፈስን ይበልጥ የሚያድሱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የክልሉ ህዝቦች እምቅ ፀጋዎችን በጋራ ጥረት በማልማት ተደማሪ ድሎችን እንደሚቀዳጁም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡