Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በህገወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር የተሰማሩ 123 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳብ ታገደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ 123 ተጠሪጣሪዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ ተደረገ።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በዛሬው ዕለት እንዳስታወቀው፥ የተጠርጣሪዎቹ የገንዘብ እንቅስቃሴ ታግዶ የህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በሂደት ላይ ይገኛል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በህጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን እየተጠቀሙ ቢሆንም አንዳንድ አካላት ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ለማትረፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸው በክትትል ተረጋግጧል።

በተጨማሪም አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑ የክትትል መረጃው ውጤት የሚያመላክት በመሆኑ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

አገልግሎቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት የህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ተግባርና ሌሎች መሰል የወንጀል ድርጊቶች ላይ ተሳታፊ በሆኑ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version