Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በውጣ ውረድ የተገኘው ትልቁ ክብር – ኦስማን ዴምቤሌ…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኦስማን ዴምቤሌ ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ ዳግም ከፍ ባለበት ፓሪስ የ2025 የባሎንዶር አሸናፊ በመሆን የወርቅ ኳሱን የግሉ አድርጓል።

ለዚህ ክብር የደረሰበት የእግር ኳስ መንገድ እንደ ብዙዎቹ የእግር ኳስ ከዋክብት የኦስማን ውጣ ውረድ የተለየው አልነበረም።

ዴምቤሌ በፈረንጆቹ 1997 ነበር በሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ ኖርማንዲ ግዛት ኢቭሪው ከተማ በምትገኘው ላ ማዴሊን መንደር የተወለደው።

ስለተጫዋቹ የሚተርከው የዘ አትሌቲክ ዘገባ፥ ዴምቤሌ እንደ ዴቪድ ቤካም፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ስቴቨን ጄራርድን የመሳሰሉ የእግር ኳስ ከዋክብትን እያደነቀ ማደጉን ያትታል።

በ7 አመቱ ኤ ኤል ኤም ኢቭሪው የተባለውን የታዳጊዎች ቡድን የተቀላቀለ ሲሆን፥ በዚያም በተለይም የተጋጣሚ ተጫዋቾችን የሚያልፍበት መንገድ ያስደምመው እንደነበር የወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ተናግሯል።

በፕሮፌሽናል ክለቦች እይታ ውስጥ ለመግባት ብዙ ጊዜ ያልፈጀበት ዴምቤሌ በ12 አመቱ በሬን ክለብ መልማዮች ተመርጦ የክለቡን አካዳሚ ተቀላቀለ።

ከዚያም በ18 ዓመቱ ዋናውን ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ በ2015/16 የውድድር አመት በሊግ-1 ለሬን 26 ጨዋታዎችን አድርጎ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር፥ አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

በውድድር አመቱ መጨረሻ ከሊግ-1 ወደ ቡንደስሊጋው አቅንቶ ቦሩሺያ ዶርትመንድን ተቀላቀለ።

በሁለቱም እግሮቹ በእኩል ብቃት መጫወት በመቻሉ በብዙዎች ዘንድ የሚደነቀው ተጫዋቹ፥ ከአንድ አመት የዶርትመንድ ቆይታ በኋላ ወደ ባርሴሎና ተዘዋወረ።

በ105 ሚሊየን ዩሮ መነሻ የዝውውር ሂሳብ የካታላኑን ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ በወቅቱ ከኔይማር ጁኒየር ቀጥሎ ውዱ ተከፋይ መሆን ችሎም ነበር።

ሆኖም የካምፕ ኑ የስድስት አመታት ቆይታው በጉዳትና ከሜዳ ውጭ ባሉ ምክንያቶች በውጣ ውረዶች የተሞላ ነበር።

የቢቢሲ ስፖርት ጸሃፊው ጉሌም ባሌግ፥ ዴምቤሌ እንዴት ዳግም ወደ ትክክለኛው የስኬት መንገድ ተመለሰ በማለት ሰፋ ያለ ሀተታ አስነብቧል።

በባርሴሎና ባጋጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት በድምሩ ከ780 በላይ ቀናት ከሜዳ የራቀው ተጫዋቹ ከጉዳቱ ባሻገር በዲስፕሊን ምክንያት በተደጋጋሚ በክለቡ ለቅጣት ተዳርጓል።

ኦስማን ዴምቤሌ በፈረንጆቹ 2021 ከሞሮኳዊት ፍቅረኛው ጋር ትዳር መስርቶ የልጅ አባት ከሆነ በኋላ በእግር ኳስ ህይወቱ ለውጦች መምጣታቸውን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።

አባትነት ህይወትን በተለየ መንገድ እንዲያስብ አድርጎታል የሚለው የቢቢሲ ስፖርት አምደኛው፥ ለዛሬው የእግር ኳስ ስኬቱ ወሳኝ እጥፋት እንደነበርም ይገልጻል።

ዴምቤሌ ወደ ፈረንሳይ ተመልሶ ፒኤስጂን ከተቀላቀለ በኋላ አሁን ላይ ለክለቡ ታሪካዊ የሻምፒየንስ ሊግ ስኬት ቁልፍ ተጫዋች መሆን ችሏል።

የፓሪሱ ክለብ ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒየንስ ሊጉ ባለክብር ሲሆን ከፓሪስ በስተምዕራብ በ96 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ኢቭሪው የተወለደው ዴምቤሌ የውድድሩ ኮከብ መባሉ አይዘነጋም።

ባለፈው የውድድር አመት በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 54 ጨዋታዎች 33 ግቦችን አስቆጥሮ 15 ግብ የሆኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ በማቀበል በ48 ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

ትናንት ምሽት በፈረንሳይ ፓሪስ በተከናወነው የ2025 የባሎንዶር የሽልማት ስነ ስርዓት የወርቅ ኳሱን ከብራዚላዊው ኮከብ ሮናልዲንሆ ጎቾ እጅ ተቀብሏል።

በምሽቱ የሽልማት ስነስርዓት ላይ በእንባ በታጀበው ንግግሩ፥ በዚህ ቦታ ተገኝቼ ይህን ሽልማት ከሮናልዲንሆ እጅ መቀበል ለእኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ይህን የምገልጽበት ቃላት የለኝም፡፡ በፒኤስጂ ለተሰጠኝ እድል ማመስገን እፈልጋለሁ ሲል ተደምጧል፡፡

ያለፈባቸው መንገዶች ቀላል እንዳልነበሩ ገልጾ፥ ቤተሰቦቹ በተለይም ደግሞ እናቱ ላደረጉለት ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ዴምቤሌ ከዚህ ክብር አስቀድሞ በፈረንሳይ ሊግ-1 በ21 ግቦች የወርቅ ጫማውን የግሉ ማድረጉ ይታወሳል።

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version