Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል የውሃ ኃብትን አሟጦ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነመራ ቡሊ በክልሉ ያለውን የውሃ ኃብት አሟጥጦ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው አሉ።

በክልሉ ጅማ ዞን ቦቶር ጦላይ ወረዳ በኤገን ወንዝ ላይ ከ406 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የፊና መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ ነመራ ቡሊ እንዳሉት፤ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል።

በዘርፉ ከሚሰሩት ስራዎች መካከል አንዱ የውሃ ሃብትን አሟጥጦ ጥቅም ላይ ማዋል መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የመስኖ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ መስኖ እና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ ግርማ ረጋሳ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ የተጀመሩ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁን 35 ያህል የመስኖ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ባጠረ ጊዜ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለግንባታ ሶስት ዓመት የወሰደው የፊና መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከ400 ሄክታር መሬት በላይ እንደሚያለማ ጠቅሰው፤ በፕሮጀክቱ ከ800 በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያሉት።

በአብዱረህማን መሀመድ

Exit mobile version