Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቴክኖሎጂ በመታገዝ የኢትዮጵያን የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የእንስሳት ሀብት ቴክኖሎጂን ማዕከል ባደረገ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡

በሰው ሰራሽ ዘዴ የተደገፈ እንስሳትን የማዳቀል ፕሮግራም የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው እለት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ተከናውኗል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በተያዘው አመት ከ5 ሚሊየን በላይ ዝርያቸው የተሻሻሉ እንስሳትን ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ለማድረስ ታቅዷል።

በእንስሳት ውጤት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ የታመነበት በቴክኖሎጂ የታገዘው እንስሳትን የማዳቀል ስራው በሀገር አቀፍ ደረጃ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ተግባሩን ወደ ቆላማ አርብቶ አደር አካባቢዎች በማስፋትም ከወተት ምርት ባሻገር የስጋ ምርት ላይ ተጨባጭ ለውጦች እንዲመዘገቡ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፥ በክልሉ ባለፉት ስድስት አመታት በሰው ሰራሽ ዘዴዎች የተዳቀሉ እንስሳትን ቁጥር ለመጨመር የተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢኒሼቲቩ ወደስራ ሲገባ ቁጥራቸው ከ245 ሺህ ባልበለጠ የወተት ላሞች እንደነበር አስታውሰው፥ እስካለፈው ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በወተት ምርት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸው፥ በክልል ደረጃ በ2012 ዓ.ም የነበረውን 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ሊትር ዓመታዊ የወተት ምርት በ2017 ዓ.ም ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ሊትር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህንን አሰራር በንቅናቄ መልክ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ለመተግበር ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ኃላፊው፥ በተያዘው አመት 2 ነጥብ 6 ሚሊየን እንስሳትን በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር እንዲወለዱ ለማስቻል ግበአቶችን የማቅርብ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በነገዎ ብዙነህ

Exit mobile version