Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና ኬንያ ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከ62 ዓመት በኋላ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ለሁለተኛ ጊዜ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የኬንያ መከላከያ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪሪ ተፈራርመዋል።
ሁለቱ ወገኖች በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የሁለትዮሽ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው በጋራ መስራት በሚቻልባቸው መስኮች ወታደራዊ የትብብር ስምምነት የተፈራረሙት።
ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ስራዎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ሀገራቱ በመካከላቸው ያለው ግንኙነትና መተማመን በሚያድግበት ወቅት የሚፈፀም ነው፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በወቅቱ እንዳሉት፥ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው የኢትዮጵያ እና ኬንያ መከላከያ ተቋማት በተለያዩ ወታደራዊ መስኮች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከኬንያ ጋር በጋራ ወታደራዊ ልምምድ፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በድንበር ደህንነት እና በሌሎችም ተያያዥነት ባላቸው ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተፈራርመናል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ሌተናል ኮሎኔል ውብሸት ቸኮል ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
በስምምነቱ ከሀገራቱ በተጨማሪ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በርካታ ስራዎችን አብረን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
ለእርሳቸውና ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገላቸው ደማቅና የሞቀ አቀባበል ምስጋና ያቀረቡት ጄኔራል ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪሪ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ እና ኬንያ ግንኙነት ከታሪክ ባለፈ በባህል፣ ህዝብ ለህዝብ እና በጂኦግራፊ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ኬንያ ያደረጉት ወታደራዊ ስምምነት ከሀገራቱ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋትም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀው፤ ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በትብብር ለመስራት የኬንያ መከላከያ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version