Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል።

ሚኒስትሩ በቻይና ኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሊ ሊቸንግ የተመራ የቢዝነስ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩበት ዕድል ተፈጥሯል።

ቻይና የኢትዮጵያ አጋር በመሆን ለዓመታት መቆየቷን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት የተመቸ ሥነ ምህዳር ፈጥራለች ብለዋል።

ቻይና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በመንገድና ባቡር መሰረተ ልማት በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እድገት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ኢትዮጵያን የቀጣናው የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ለጀመርነው ስራ አጋዥ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻልና የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻሏን ገልጸው÷ ኢትዮጵያን ተገማችና ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የክህሎት ልማት፣ ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ኢንዱስትሪን ዕውን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት የቻይና ባለሀብቶች ሚና የላቀ መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን መደገፍ የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ መዘርጋቷን ጠቅሰው÷ ቻይናን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይና የኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሊ ሊቸንግ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ አድንቀው÷ ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብር እያደገ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ÷ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እሴት በሚጨምሩ የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች ላይ በስፋት እንደሚሳተፉ መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version