Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሄቨን-1 የተሰኘ የመጀመሪያው የግል የጠፈር ጣቢያ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለማችን የመጀመሪያ የሆነው ሄቨን-1 የተሰኘ የንግድ የጠፈር ጣቢያ ሊጀመር ነው።

ላለፉት 25 ዓመታት ምድርን በመዞር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (ISS) በፈረንጆቹ 2030 አካባቢ አገልግሎት መስጠቱን የሚያቋርጥ ሲሆን÷ ጊዜው መቃረቡን ተከትሎ የአሜሪካው ብሔራዊ ኤሮኖቲክስ እና የጠፈር አስተዳደር (NASA) የጠፈር ጣቢያ አገልግሎትን ከንግድ የጠፈር ጣቢያዎች ለመግዛት ከተለያዩ የዘርፉ ተቋማት ጋር መስራት ጀምሯል።

ከእነዚህ የግል ኩባንያዎች መካከል በካሊፎርኒያ የተመሰረተው እና ቫስት የተሰኘው ኩባንያ ከስፔስ ኤክስ ጋር በመተባበር ሄቨን-1 የተሰኘ የመጀመሪያ የሆነውን የንግድ የጠፈር ጣቢያ ለማስጀመር እየሰራ እንደሚገኝ የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመላክቷል።

ሄቨን-1 የተሰኘው የጠፈር ጣቢያ በፈረንጆቹ ግንቦት 2026 ፋልኮን 9 የተሰኘውን ሮኬት በመጠቀም የጣቢያውን አገልግሎት ለማስጀመር መታቀዱና ለሦስት ዓመታት በምህዋር ውስጥ እንዲቆይ ተደርጎ መሰራቱ ተመላክቷል።

የቫስት ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማክስ ሃኦት ሰዎችን ወደ ምህዋር የሚልክ እና በሰላም እንዲመለሱ የሚያደርግ እውነተኛ የጠፈር ጣቢያ ኩባንያ መሆን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ጣቢያው በጠፈር ቆይታው ለጠፈርተኞች የግል የመኝታ ክፍሎች፣ የጋራ ጠረጴዛ፣ በስታርሊንክ የተደገፈ ኢንተርኔት እና አነስተኛ የሳይንስ ላቦራቶሪ እንደሚያቀርብ ገልጸው÷ ቅንጡ ሆቴል እንዲሆን ተደርጎ አለመገንባቱን ተናግረዋል።

ኩባንያው በምድር ላይ ለሙከራ የሚያገለግል የሄቨን-1 ሞዴልን ገንብቶ ማጠናቀቁን እና ወደ ጠፈር የሚመጥቀውን ትክክለኛ ሞዴል በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከፊታችን ያለው ቁልፍ ምዕራፍ የመጀመሪያ ተጓዦችን ማሳወቅ እንደሆነ ጠቅሰው÷ የጠፈር ኤጀንሲዎች፣ ሀገራት፣ የግል እና የገንዘብ ድጋፍ ያላቸው ግለሰቦች የኩባንያው ደንበኞች ሆነው እንደሚካተቱ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የሄቨን-1 ተልዕኮ ወደ ፊት የዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ተተኪ እንዲሆን የታቀደለትን ሄቨን-2 የተባለውን ትልቅ የጠፈር ጣቢያ ለመገንባት እንደ መጀመሪያ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።

የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ፍሬድሪክ ሻርመን በበኩላቸው÷ ሄቨን-1 ፕሮጀክት የሚሳካ ከሆነ ተልዕኮው የጠፈር ጣቢያዎች የመንግሥት ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆኑ የህዋ ኢኮኖሚ ንግድ አካል የሆኑበት አዲስ ዘመን መጀመሩን ማሳያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version