አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራት እና ፍጥነት በማከነወን አበረታች ውጤት ተመዝግቧል አሉ፡፡
የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት የልማት ፕሮጀክቶች የመስክ ምልከታ ሪፖርት ላይ የፕሮጀክት ባለቤት ተቋማት በተገኙበት ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት÷ የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራት እና ፍጥነት በማከናወን አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ደረጃን የማስጠበቅ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመው÷ በዚህም የጥራት ጉድለት፣ የግብዓት አጠቃቀም ችግር፣ የክትትል እና የተቋራጮች ብቃት ማነስ መታየታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም የጥራት ደረጃ ውስንነት የተስተዋለባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እና ፍጥነት እንዲከናወኑ ለማስቻል ባለቤት ተቋማት ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለሚከሰተው የጥራት ጉድለት እና መጓተት ተጠያቂ መደረግ ያለባቸው አካላት በህግ እንደሚጠየቁ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።