Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊት …

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ አንዱ ነው፡፡

መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ደሙን አፍስሶ፣ ስጋውን ቆርሶ ዓለምን ያዳነበት የክርስቶስ ዙፋን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ክብርና ቦታ እንደሚሰጠው የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡

መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ የስምሪት ኃላፊ ናቸው፡፡

እንደ መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ገለጻ÷ ቤተክርስቲያን የመስቀል በዓልን ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ዓለምን ማዳኑን፣ መስቀል በክርስቶስ ደም የከበረ መሆኑንና ስግደትም እንደሚገባው ታስተምራለች፣ በተግባርም ትገልጻለች፡፡

የመስቀል በዓል ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ለሰው ልጆች መዳን ሲል የገለጸውን ፍቅር እና ያሳየው ርሕራሄ መገለጫ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

መስቀል ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ዓለምን ካዳነበት በኋላም በኢየሩሳሌም ድውይን በመፈወስ፣ የሞተን በማስነሳት፣ ለምጻምን በማንጻት፣ ጎባጣን በማቅናት የመዳን ምልክት ሆነ፡፡

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ገቢረ ተዓምራት ማድረጉን ያልወደዱ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም መስቀሉን ለመሠወር ወሰኑ፡፡

በዚህም ጉድጓድ ቆፍረው የመዳን ምልክት የሆነውን መስቀል ቀበሩት፤ የተቀበረበትን ቦታም ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያና ማከማቻ አደረጉ፡፡

የመስቀሉ ማዳን እና ብርሃን በልቦናቸው የተገለጸላቸው ክርስቲያኖች እየበዙ መምጣታቸውን ተከትሎም መስቀሉን መፈለግ ጀመሩ፤ ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከልም ንግሥት እሌኒ አንዷ ናት፡፡

ንግሥት እሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ ለእግዚአብሄር የተሳለችው ስለት በመድረሱ ክብረ መስቀሉ ያለበትን ቦታ መመርመርና መጠየቅ ጀመረች፡፡

መስቀሉን ስትፈልግም ሁለት አካላት እንዳገዟት የሚያወሱት መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ÷ አንደኛው ከታሪክ አዋቂ ሰዎች መካከል ኪራኮስ ከሶስት ተራራዎች በአንዱ የክርስቶስ መስቀል ተቀብሯል ተብሎ እንደሚነገር አመላክቷታል ይላሉ፡፡

ንግሥት እሌኒ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየትም በእግዚአብሔር መልዓክ ቅዱስ ሚካዔል እርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣን በመጨመርና በማቃጠል ለሰባት ቀናት ሱባዔ መያዟን ያስረዳሉ፡፡

በዛሬው ዕለት በደመራው ዙሪያ የሚደርሰው ጸሎት እና የሚዜመው ዜማም ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው የሚያብራሩት፡፡

ንግሥት እሌኒ ደመራውን አስደምራ ስታስለኩሰውም እጣኑ ወደ ሰማይ ሄዶ ከሶስቱ ተራሮች መካከል መስቀሉ ያለበት ተራራ ላይ በማረፍ አመላከተ፤ ጢሱ ደግሞ ወደ ሰማይ ደርሶ መስቀሉ ወዳለበት ቦታ መስገዱን ያስረዳሉ፡፡

በቀጣይም ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ቁፋሮ እንዲጀመር አዘዘች፡፡ በዚህ ዕለትም እዮሃ ይባላል፤ በተለይም በገጠሩ አካባቢ እዮሃ አበባዬ … እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ የሚባለው ለዚህ ነው ይላሉ፡፡

ከሰባት ወራት ቁፋሮ በኋላም መጋቢት 10 ቀን የማዳን፣ የብርሃን እና የሰላም ምልክት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘቱ ተበሰረ፡፡

ከባሕላዊ እሴቱ አንጻርም መስቀል ሰላም የታወጀበት፣ ፍቅር የተሰበከበት በዓል በመሆኑ ሁሉም በአንድነት የሚያክብረው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የመስቀል በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ወቅት የሚከወኑ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶች ቀልብን የሚስቡ ናቸው ይላሉ፡፡ በዚህም በርካታ ቱሪስቶች በመምጣት የመስቀል በዓልን እንደሚታደሙ አንስተዋል፡፡

ወቅቱ ወርሃ መስከረም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እቅድ የምናቅድበት፣ መልካም ነገር የምንመኝበት እና ሌሎች ነገሮችን ለማሳካት ተስፋ የምንሰንቅበት ነው፡፡

ደመራው ሲበራ ብርሃን አለ የሚሉት መጋቤ ብሉይ አዕምሮ፤ ያ ብርሃንም ለእያንዳንዳችን ብሎም ለሀገራችን ተስፋ መሆኑን አውቀን በአንድነት፣ በፍቅርና በሰላም ልናከብረው ይገባል ብለዋል፡፡

መልካም የመስቀል ደመራ በዓል!

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version