Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

 በትምህርትና ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ በትምህርት እና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ የማፍራቱ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው አሉ።

የኦሮሞ ጥናት ማህበር በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያሳተማቸው አራት መጽሐፍት ተመርቀዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማጎልበት እና ጠንካራ ስርዓት መገንባት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚተገበሩ ስራዎች ናቸው።

በተለይም ትውልዱን በትምህርት እና በቴክኖሎጂ ማብቃት የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የክልሉ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያቋቋማቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ስኬታማ ሆነዋል ብለዋል።

የኦሮሞ ጥናት ማህበር እውቀትን ማዕከል በማድረግ የሚሰራቸው ሥራዎች የሚበረታቱ እንደሆነ ገልጸው፤ የክልሉ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ማህበሩ ትውልዱ ታሪኩን እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣ ዛሬ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ማቅረብና የወደፊቱን መተንበይ ላይ እንዲያተኩር አስገንዝበዋል።

የኦሮሞ ጥናት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ በቀለ ጉተማ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ማህበሩ የኦሮሞ ባህል፣ ታሪክ እና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ጥናቶችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም የህዝብ አኗኗር እና ነባር እሴቶችን ማጥናትና ለትውልድ ማሳወቅ እንዲሁም የህዝቡን የኢኮኖሚ ሁኔታ በመቃኘት የመተንተን ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቁት አራቱ መጻህፍትም ትውልዱ እውቀትና እውነት ላይ ተመስርቶ እንዲወያይ፣ እንዲነጋገርና እንዲግባባ የሚያግዙ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version