አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በማካሄድ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር አጀንዳ የማሰባሰብ ምክክር በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው÷ በሂደቱ በውጭ ከሚኖሩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር በገጽ ለገጽና በይነ-መረብ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ከሚኖሩት ጋር በገጽ ለገጽ ገንቢ ምክክር ማካሄድ ተችሏል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በሌሎች ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ አጀንዳቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፤
በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደትም በውጭ የዳያስፖራ ማህበሰረብ አባላት ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በአጀንዳነት እያቀረቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የፖለቲካ ዓላማቸውን በትጥቅ ለማሳካት በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡