Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመኸር ሰብል ምርት ለመሰብሰብ የአማራ ክልል ዝግጅት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በመጪዎቹ ወራት የሚደርሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ።
በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምሳሉ ጎባው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በመኸር እርሻ ወቅት የተዘሩ ሰብሎች ምርት መሰብሰቢያ ጊዜ ደርሷል።
የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ ኮምባይነሮችንና የሰብል መፈልፈያ ማሽኖችን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ በመምጣቱ አርሶአደሮች የግብርና ስራዎቻቸውን በተሻለ መልኩ ማከናወናቸውንና የተዘሩት ሰብሎችም በጥሩ ይዘት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በዚህም በክልሉ 2017/18 የመኸር ወቅት 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈኑንና 187 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
ከመኸር እርሻ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት ባለፉት ጊዜያት የአረም መድኃኒትና ኬሚካል የመርጨት ስራዎች መሰራታቸውን እንዲሁም ለሰብሎቹ አስፈላጊ የክብካቤ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የግብርና ስራ በአንድ ወቅት የሚወሰን አለመሆኑን አንስተው÷ በመኸር ወቅት ለአርሶ አደሮች 200 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ 163 ሺህ ኩንታል መሰራጨቱን ገልጸዋል።
ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን እስካሁን ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በክልሉ የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት አመርቂ ውጤት የታየበት መሆኑን አንስተው÷ በ2017 ዓ.ም 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል።
በሰሊጥ ምርት የክልሉን አቅም ከማጎልበት አንፃር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና በባለሙያዎች ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው÷ 443 ሺህ 97 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
Exit mobile version