አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አረርቲ ከተማ አስተዳደር በአረርቲ ማርያም ቤተክርስቲያን በግንባታ መወጣጫ መደርመስ አደጋ የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሶ፥ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገልጿል፡፡
አገልግሎቱ ባስተላለፈው የሀዘን መግለጫ መልዕክት፥ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን እንዲሁም በሕክምና ላይ ለሚገኙት በፍጥነት ማገገምን ተመኝቷል፡፡
ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ ግንባታ ላይ መሆኗን ጠቅሶ፥ ከትልልቅ ግድቦች ጀምሮ እስከ አነስተኛ የግለሰብ ቤት አጥር ድረስ ያሉ ግንባታዎች ሲሠሩ ደኅንነትን ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ነው አገልግሎቱ ያስገነዘበው፡፡
በግንባታ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ ጉብኝቶችም የሥራ ላይ ደኅንነት መርሆዎችን እንዲጠብቁ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡