Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢሬቻ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አሉ።
የሀገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ የአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ ሸገር ከተማ ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታና ደህንነት አካላት እና አመራሮች በዓሉ በሚከበርበት እና ሊከናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ እንዳሉት፤ ህዝብ በታላቅ ድምቀት የሚያከብረው የኢሬቻ በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህም በቂ የሰው ኃይል በመመደብ የቅድመ ወንጀል መከለከል እና ቁጥጥሩ ስራ በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በዓሉ በስኬት እንዲከበር የዝግጅቱ አስተባባሪዎችና የበዓላቱ ታዳሚዎች ሚና የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፤ በዓሉ ለአዲስ አበባ ከተማ ድምቀት ከመሆኑ ባሻገር የህዝብ አብሮነት ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከበዓሉ አከባበር ኮሚቴዎች፣ ከኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት፣ ከሀደ ስንቄዎች፣ ከፎሌዎች ጋር በመቀናጀት በዓሉን የሚመጥን የጸጥታ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች በዓሉን ለማክበር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታዳሚ ወደ መዲናዋ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖር አስገንዝበዋል።
እንደሁልጊዜው ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀው፤ ከበዓሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ቁሳቁስ ይዞ ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሰላም ሰራዊት አባላት በቂ ግንዛቤ ይዘው ወደ ስራ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በፍጥነት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ መጠየቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘት በፌዴራል ፖሊስ የለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ ጨምሮ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም ይቻላል።
Exit mobile version