Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮሚሽኑ በሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን ለመፍጠር የጀመረው ስራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል – አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን ለመፍጠር የጀመረው ስራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ።

አፈ ጉባኤው ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፥ ባለፉት ዓመታት በምክክር ሂደቱ የተከናወኑ አጀንዳ የማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ተግባራት አፈፃጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

ከ2016 ዓም ጀምሮ ሀገራዊ የምክክር ሂደት የዝግጅት ምዕራፍ ክንውኖችን፣ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ተግባራትን በሪፖርታቸው ዳስሰዋል፡፡

በዚህም በእስካሁኑ ሂደት በ11 ክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ተግባራት ማከናወን እንደተቻለ ነው ያነሱት።

በትግራይ ክልልም በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ማካሄድ የሚያስችሉ ቅድመ ውይይቶች መካሄዳቸውን አብራርተዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መካሄዳቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር የገጽ ለገጽ እና የበይነመረብ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ፣ በካናዳ ቶሮንቶ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሌሎች ከተሞች አጀንዳ የማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ስኬታማ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በስዊድን የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ምክክር እየተካሄደ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ በቀጣይ ሳምንት ይኸው ስራ በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፥ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶችን በምክክር መፍትሔ ለመስጠት ጥልቅ ፍላጎት እንዳላቸው በተግባር ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን ለመፍጠር የጀመረው ሥራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ገልጸው፥ በቀጣይም ኢትዮጵያውያን በኃላፊነት መንፈስ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የሚያደርጉትን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

የሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት ለኮሚሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version