Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተጨማሪ 3 ሺህ 350 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተዋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተሻሻለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤት እና በተስተካከለው የፊዝክስ ውጤት ተጨማሪ 3 ሺህ 350 ተማሪዎች አልፈዋል አለ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት።

ትምህርት ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና አማካይ ውጤታቸው 49 ነጥብ 50 እስከ 49 ነጥብ 99 በመቶ ያመጡ ተማሪዎች ወደ 50 በመቶ እንዲጠጋጋ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረትም የ2017 ትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤት ከ300 ወደ 297 ዝቅ ብሏል፡፡

በተጨማሪም በበይነ መረብ በተፈተኑ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የፊዚክስ ውጤት ወደ መቶኛ ያልተቀየረላቸው እንዲሁም ወደ መቶኛ ሲቀየር በነጥብ ቤት የነበሩ ቁጥሮች ያልተደመረላቸው ተማሪዎች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም ተማሪዎቹ ተያያዥ መረጃዎች ላይ ቅሬታቸውን አቅርበው ውጤታቸው መስተካከሉ ነው የተገለጸው፡፡

ይህን ተከትሎም 3 ሺህ 350 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ያመጡ ሲሆን ÷ በ50 ከመቶና በላይ ያመጡ አጠቃላይ ተፈታኞች ቁጥርም 52 ሺህ 279 ደርሷል፡፡

ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር በመቶኛ ሲገለጽም 8 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ መመዝቡን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version