አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ማዕከላት የሚገኙ ዜጎች ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጡ እየተሰራ ነው።
ከሰሞኑ በክልሉ 18 ወረዳዎች የተከሰተው ጎርፍ ከ67 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ላይ የጎዳት አድርሷል፡፡
የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና እርዳታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት የነዋሪዎቹ ህይወት በጎርፍ አደጋ እንዳይጠፋ በፌደራልና በክልሉ መንግስት ርብርብ ተደርጓል።
ሆኖም የነዋሪዎችን ህይወት ከጎርፍ አደጋው የማዳን ስራው የኮሮና ቫይረስን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማከናወኑ ላይ ክፍተት ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ ከ12 ወረዳዎች የጤና ኤክስቴንሽን እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን ወደ መጠለያ ማዕከላቱ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ የተፈናቃዮቹን ጤና ሁኔታ ክትትል የማድረግ ስራ ተጀምሯልም ነው ያሉት።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ በበኩላቸው በክልሉ ጊዜያዊ ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ እንዲቋቋም በማድረግ በጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች እየተንቀሳቀሱ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የቫይረሱን አስከፊነት በተመለከተ ግንዛቤ መፍጠር ቢቻልም የአስተሳሰብ ለውጥ በሚፈለገው ደረጃ ባለመኖሩ በስፋት መዘናጋት ይታያል ነው የሚሉት ምክትል የቢሮ ሃላፊው።
በዚህም ለኮሮና ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች፣ ህጻናትንና ነብሰጡሮች በጎርፍ ምክንያት ከተፈናቀሉ ዜጎች በመለየት የተለየ ክትትል በጤና ባለሙያዎች እየተደረገላቸው ይገኛል።
በሁሉም ጊዜያዊ የመጠለያ ማዕከላት ከነገ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይጀመራል ነው የተባለው፡፡
ምርመራውን ተከትሎ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ተፈናቃዮች ካሉ በመለየት ክትትል እና ህክምና ለማድረግ የሚያስችሉ ማዕከላትም ተቋቁመዋል።
ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ የሚሆን ከሆነም የጎርፍ አደጋው ከተከሰተባቸው 12 ወረዳዎች ውጭ በሚገኙ ሆስፒታሎች ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል ነው የተባለው።
በበላይ ተስፋዬ

