አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ቃልን በተግባር በመግለጽ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እያሳካ ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
መንግሥት ቃልን በተግባር በመግለጽ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እያሳካ ነው ፡፡
መንግሥት ከለውጡ እውን መሆን ጀምሮ የገባቸዉን ቃሎች እየፈጸመ፣ ኢትዮጵያን ወደሚገባት ከፍታ ለማውጣት የብልጽግና ጉዞዉን እያሳመረ ቀጥሏል፡፡
ከዓመታት በፊት በ2018 ዓ.ም ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን ሽግግር እናደርጋለን የሚል ርዕይ የያዘው ቃል የኢፌዴሪ መንግሥት ቃሉን በተግባር እየገለጸ ይገኛል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት ተጉዘናል፤ በመኸር እርሻ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በበጋ መስኖ በመታገዝ ሰፋፊ ድሎች ተመዝግበዋል፡፡
የከተሞቻችን ገጽታ ለመቀየር በተሠሩ ሥራዎች ከ70 በላይ ከተሞች ገጽታቸዉ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ የከተሞቹ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዐት፣ የእግረኛ እና ተሽከርካሪ መንገድ አጠቃቀም፤ እንደ ውኃ፣ ስልክ፣ ኤሌክትሪክና መሰል አገልግሎቶች መሥመር ዝርጋታ በከተሞች የኮሪደር ሥራ በእጅጉ እንዲዘምኑ ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው፡፡
የሥነ ንጽሕና እሳቤ እና ሥርዐት በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞቻችን የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
በታዳሽ ኃል አቅርቦት ረገድ ለማሳካት የተቀመጠዉን ግብ ታላቅ የትርክት ለውጥ በፈጠረዉ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አማካኝነት እውን ሆኗል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለሌላዉ ዓለም ያለሰባራ ሳንቲም የውጭ ዕርዳታ በጋራ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ሕዳሴ ግድብ ትዕምርታችን ነው፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሌሎች የገዘፉ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ፣ በመጠናቀቅ ላይ የነበሩም እንደሚመረቁ ቃል መግባታቸዉ ይታወሳል፡፡
እነሆ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚፋጥኑ እንደ ተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተመረቁ፤ ከተመረቀዉ በብዙ እጥፍ ፕሮጀክት ተበሰረ፤ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ እና የዐፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመሩ፡፡
ኢትዮጵያ የኑክሊየር ኃይልን ለሰላማዊ ልማት ለመጠቀም ስምምነቶችን ተፈራረመች፤ ከዓለማቀፍ ተቋማትም ይሁንታን ተቸረች፡፡ እነዚህ ሁሉ ቃልን በተግባር የመለወጥ ልምድ የወለዳቸው፤ የሕዝብ እና ዓለማቀፍ ተቋማትን እምነት ማግኘት የተቻለባቸው የመንግሥት ጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡
መንግሥታችን አሁንም በተመዘገቡ ስኬቶች ረክተው የሚተኛ መንግሥት አይደለም። የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከስር ከስር እያሳካ አዳጊ ፍላጎቶችን እያዋለደ ለላቀ ብልጽግና መትጋቱን ይቀጥላል፡፡
ለትውልድ ምንዳን እንጅ ዕዳን አናወርስም ባለዉ መሠረት በልጆቿ የጋራ ጥረት የበለጸገችና በምሳሌነት የምትጠቀስ ኢትዮጵያን የመገንባቱ ጥረት በላቀ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ትጋት ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ ዐዲሲቷ የተስፋ ዓድማስ!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት