አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል በተከናወነ ተግባር ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል።
‘በባለቤትነት ላይ የተመሰረተ እውቅናና ተጠያቂነት ለጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ’ በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ ዓመታዊ የጤና ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በጉባኤው ላይ እንዳሉት፤ በ2017 በጀት ዓመቱ መሰረታዊ ተግዳሮቶችን በመለየት በተሰሩ ስራዎች ውጤት መጥቷል።
በዚህም የጤና ቁጥጥር ስርዓቱን ለማሻሻል በተሰራው ስራ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ጫና መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
ለዘርፉ ውጤታማነት ሁለንተናዊ ቅንጅትና ትብብር ብሎም አመራር ሰጪነት በማጎልበት በተሰራው ስራ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ ሆኗል ነው ያሉት።
የእናቶችና ህፃናት ጤናን ማሻሻል፣ የመድሃኒትና ህክምና ግብአት አቅርቦት፣ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ግንባታና አገልግሎት ላይ ተጨባጭ ውጤት ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ የጤና ስርዓት ግንባታ ማጠናከር፣ የማህበረሰቡን የጤና ባለቤትነትና ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ የማበረታቻና የተጠያቂነት አሰራር ስርዓትን መዘርጋት፣ የአፈፃፀም ውጤታማነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።