Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስን በማልማት የገቢ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስን በማልማትና የገቢ ምንጭ በማድረግ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል አሉ።
በክልሉ ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የሚገኘውን የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ አካባቢ ለማልማት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የፕሮጀክቱ ወጪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ እንዲሁም ከባለሀብቱና ከአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ይሸፈናል።
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ መካነ ቅርሱ ረጅም ዕድሜ ቢኖረውም በተገቢው መንገድ ለምቶ ለጎብኚዎች ምቹ ሳይሆን ቆይቷል።
በዚህም ከቱሪዝም መገኘት የነበረበትን ገቢ እንዳላስገኘ ጠቅሰው፤ ቅርሱን በማልማትና የገቢ ምንጭ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ በበኩላቸው፤ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ እንደሚከናወንለት መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የግንባታ ሥራው ሆቴል፣ የተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎችን እንዲሁም የግብይት ማዕከላትንና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን አካትቶ እንደሚከናውንም ተናግረዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን፤ በዞኑ የሚገኙትን ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
Exit mobile version