አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሕዝብ የቀረበና ለሕግ የታመነ አስተዳደር ወደ ብልጽግና ለሚደረግ ጉዞ ወሳኝ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ሁለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን እንደጀመሩ በማብሰር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የተጀመረው የኢትዮጵያ የማንሠራራት ምዕራፍ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ መንግሥት በ2018 በጀት ዓመት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
አሁን ላይ ከሥርዓት መለዋወጥ ጋር የማይፈርሱ ነጻ፣ ገለልተኛና ሕዝባዊ ብሔራዊ ተቋማት ለመፍጠር መንግሥት ፅኑ መሰረት መጣሉን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ ዓመትም ቀጣይነት ባለው ዕድገት አንድነታችንና ደህንነታችን በማይናወጥ ደረጃ ለማድረስ መንግሥት የተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት።
ብሔራዊ የፀጥታና የደህንነት ተቋሞቻችን የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ፣ ሀገርን የሚያሻግሩና ሀገር አስቀጣይ ተቋማት እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
ሰላም የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ÷ እርቅና የሰላም መንገድን በመከተል የኢትዮጵያን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል
በኃይል ስልጣንን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን በሃይል ለመቋጨት መንግሥት ዝግጅቱም አቅሙም እንዳለው ጠቅሰው ÷ ይሁን እንጂ መንግሥት በብልሃትና ትዕግስት ለነገ ሰላም የሚያተርፍ አካሄድን እንደመረጠ አስገንዝበዋል፡፡
ለሕዝብ የቀረበና ለሕግ የታመነ አስተዳደር ወደ በለጸገች ሀገር ለመሸጋገር ወሳኝ ነው፤ ስለሆነም መንግስታዊ አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ በቅልጥፍና የታጀበ መሆን አለበት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
መልካም አስተዳደር የመልካም ፖለቲካ ማዕዘን ድንጋይ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ ÷ የሕዝብ አገልግሎትን ለማዘመን በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ለዜጎች ዋስትና የሆነ የፍትሕ ሥርዓትን ለመዘርጋትም የሕግ አስከባሪና ፍትሕ ተቋማትን አቅም ከማሻሻል ባለፈ ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ