Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክር ቤቱ 13 አቤቱታዎች የሕገመንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ሲል ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀረቡለት አቤቱታዎች ውስጥ 13ቱ የሕገመንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ሲል ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው የሕገመንግሥት ትርጉምና የውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ መርምሮ ባቀረባቸው የውሳኔ ሃሳቦች ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም በምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል የውሳኔ ሃሳብ ባቀረበባቸውና እና ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ መክሯል።

ቋሚ ኮሚቴው በ13 ጉዳዮች ላይ ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ፤ በቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ደግፎ አጽድቋል።

በተጨማሪም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል በሰጣቸው ውሳኔዎች ቅር በመሰኘት በይግባኝ ለምክር ቤቱ የቀረቡ 92 ጉዳዮችን ቋሚ ኮሚቴው መርመሮ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም የሚል የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምጽ ደግፎ እንዳጸደቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተረፈ በዳዳ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

Exit mobile version