አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የተከበሩት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔ በዓላት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በማነቃቃት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል አለ የከተማዋ ቱሪዝም ኮሚሽን፡፡
አዲስ አበባ ባለፉት ሳምንታት በርካታ ሰዎች የታደሙባቸው የአደባባይ በዓላትን በደመቀ ሁኔታ አስተናግዳለች፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በዓላቱ በርካታ ታዳሚዎች የሚሳተፉባቸው እንደመሆናቸው መጠን እንግዶችን ለማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
የበዓላቱ ተሳታፊዎችና የውጭ ጎብኚዎች በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ ከግሉ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡
በዓላቱ በተለይም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ተሳታፊዎች ከበዓላቱ ስነስርዓቶች ጎን ለጎን በከተማዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላቱ ባሻገር በኮንፈረንስ ቱሪዝም በርካታ ስኬት መመዝገቡን ገልጸው፥ ለአብነትም በ2017 ዓ.ም 150 ያህል አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶች በመዲናዋ ተካሂደዋል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማስፋፋትና በማስተዋወቅ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን አቅም በማጎልበት ከቱሪዝም የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ