Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የወንዝ ዳርቻ ልማት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በስድስቱ የማዕከል ከተሞች የወንዝ ዳር ልማት በተቀናጀ መንገድ ለማካሄድ እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የከተሞች ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት ለማሳደግ የአዲስ አበባን የወንዝ ዳርቻ ልማት ተሞክሮ በመቀመር በትኩረት እየተሰራ ነው።

ልማቱ የክልሉን ከተሞች አቅምና ፀጋ በመግለጥ ለቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ይበልጥ ተመራጭ የሆኑ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ከተሞች ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ጠቁመዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማት እንደየከተሞቹ ነባራዊ ሁኔታ እንደሚተገበር ጠቅሰው÷ በዝግጅት ሥራው ከተሞች አስፈላጊውን የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት ጨምሮ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ዝርዝር ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በሚገኙ ሦስቱ የረጂዮ ፖሊስ ከተሞች ቀድመው የተጀመሩ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው÷ የፕሮጀክቶችን ጥራት በማሻሻልና በማጠናከር በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ይሰራል ነው ያሉት።

የወንዝ ዳር ልማቱ በርካታ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንዲሁም በከተሞች ቱሪዝምን በማነቃቃት፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የንግድ ልውውጥን በማሳለጥ እና የከተሞች የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በማጠናከር ለክልላዊና ሀገራዊ ብልጽግና ጉልህ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ተሳትፎ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች የክልሉ ከተሞች በፈጣን የለውጥ ሒደት ላይ እንዲገኙ ማስቻሉን አብራርተዋል።

ለከተሞች ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ልማት በሁሉም መስክ የተጀመሩ የከተማ ልማት ሥራዎችን ከማጠናከር ባለፈ በከተሞች ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ለይቶ በመጠቀም ዕድገታቸውን ለማፋጠንና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በክልሉ ከተሞች ዕድገትና ገጽታ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣና ባለድርሻ አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version