አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቆጣሪ ምርመራ አሠራር ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነትን መፍጠር የሚያስችል መተግበሪያ ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ጀምሮ ሥራ ላይ ያውላል፡፡
መተግበሪያው ከፍጆታ ክፍያና ከኢነርጂ ብክነት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን መቀነስ እንደሚያስችል የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በቆጣሪ ምርመራ ወቅት ለደንበኞች ግልፅነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሠራርን መፍጠር የሚያስችል ዘመናዊ የቆጣሪ ምርመራ ሥራ መረጃዎችን በሲስተም መመዝገብ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
መተግበሪያው በቀላሉ ስልክ ላይ በመጫን የቆጣሪ ምርመራ መረጃዎችን ለመመዝገብ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለሁሉም የቆጣሪ አይነቶች የሚያገለግለው መተግበሪያው ÷ በቆጣሪ ላይ የሚደረጉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ጨምሮ የቆጣሪ መረጃዎችን እንደሚመዘግብ ጠቅሰዋል፡፡
መረጃዎችን በዲጂታል መልክ ለመያዝ፣ የምስል መረጃዎች በመያዝ ሥራዎችን በቀላሉ ኦዲት ለማድረግ፣ እንዲሁም ፈጣን የሥራ ፍሰቶች እንዲኖር በማድረግ ወጪን እንደሚቀንስ አብራርተዋል፡፡
መረጃዎችን ከጂፒኤስና የቆጣሪ ምርመር ሥራው የተከናወነበት ሰዓት ጋር በማገናኘት የሚመዘግብ በመሆኑ ሥራ ከተጠናቀቀ በኃላ መረጃው ለውሳኔ ሰጪዎች አካል በድጋሚ ቢፈለግ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችልና ኦዲት ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
የቆጣሪ ምርመራው በማን እንደተሠራ፣ ምን ግኝቶች እንደተገኙ፣ መቼ ምርመራው እንደተከናወነ እንዲሁም የተገኘው ግኝትና የተወሰደውን ርምጃ መለየት ያስችላልም ብለዋል፡፡