Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በልደታቸው ማግስት የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት ማሪያ ኮሪና ማሻዶ…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዚህ ሳምንት 58ኛ ዓመት ልደታቸውን ያከበሩት ቬንዙዌላዊቷ ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና ማሻዶ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፋቸው በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል፡፡

የኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆኑት ማሪያ ኮሪና የተወለዱት በቬንዙዌላ ካራካስ ከተማ ነው፡፡

በፖለቲካው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቬንዙዌላ የላይኛው መደብ ከሚባል የማህበረሰብ ክፍል ቤተሰብ የተገኙ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ ሶሻሊስት መንግስት ኢላማ ውስጥ መግባታቸው ይነገራል፡፡

በማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ በሚያደርግ ቤተሰብ ውስጥ ማደጋቸው አሁን ላይ ለኖቤል የሰላም ሽልማት ለበቁበት የዴሞክራሲ መብት ተሟጋችነት የላቀ ሚና እንዳለው ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡

በፈረንጆቹ 1992 በትውልድ ከተማቸው ካራካስ አቴኒያ ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም በመመስረት ለጎዳና ተዳዳሪዎች እገዛ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከ10 ዓመታት በኋላ በሀገሪቱ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን በተቋቋመው ሱሜት የተሰኘ ተቋም መስራቾች መካከልም አንዷ ናቸው፡፡

ወደ ፖለቲካው ይበልጥ በመግባት በፈረንጆቹ 2010 በቬንዙዌላ በተደረገው ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት የሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ለመሆንም በቅተዋል።

በኋላም ቬንቴ ቬንዙዌላ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከመሆን ባለፈ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ አንድ በማምጣት ጥምረት እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ባለፈው ዓመት በቬንዙዌላ በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ ይፋ ካደረጉ በኋላ በምርጫው ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ለመከላከል የተለያዩ እክሎች ሲፈጠርባቸው ቆይቶ መጨረሻ ላይ ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡

ማሻዶ በተለይም በሀገሪቱ አምባገነናዊ የመንግስት ስርዓትን በመታገል ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው ይነገራል፡፡

በዚህም በቅርቡ በአውሮፓ ህብረት የተበረከተላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ሽልማት ጨምሮ ልዩ ልዩ እውቅናዎችን አግኝተዋል።

ለቬንዙዌላውያን ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ፍትሃዊና ሰላማዊ በሆነ ሽግግር ሀገሪቱን ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ሲያደርጉት የቆየው ጥረት ለሽልማቱ እንዳበቃቸው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ገልጿል፡፡

በቬንዙዌላ መንግሥት የሚደርስባቸውን አደጋ በመሸሽ ከአንድ ዓመት በላይ ተሸሽገው የሚገኙት ማሻዶ፤ ሽልማቱን እንደማሸንፍ አልጠበቅኩም ነበር ብለዋል።

ሽልማቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝባችን ስኬት ነው በማለት በተንቀሳቃሽ ምስል ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።

ሽልማቱን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማሪያ ኮሪና ማሻዶ የደስታ መግለጫ መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡

የ2025 የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ማሻዶ ከሜዳልያና ዲፕሎማ በተጨማሪ ከ1 ነጥብ 15 ሚሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version