አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሃማስ እስራኤላውያን ታጋቾችን በዛሬው ዕለት መልቀቅ ጀምሯል፡፡
ታጋቶቹ የተለቀቁት እስራኤልና ሃማስ የመጀመሪያ ዙር የጋዛ የሰላም እቅድ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ሃማስ እስካሁን በሕይወት ያሉ እና በዛሬው ዕለት የሚለቀቁ የ20 እስራኤላውያን ታጋቾን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
አሁን ላይም የመጀመሪያዎቹ ሰባት ታጋቶች መለቀቃቸውን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ማረጋገጡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቀሪዎቹን 13 እስራኤላውያን ታጋቾችን ለመረከብ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር በደቡብ ጋዛ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
በምላሹም እስራኤል 1 ሺህ 950 በላይ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመልቀቅ ዝግጅት ማጠናቀቋ ነው የተገለጸው፡፡
በሌላ በኩል ለእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት የአንበሳውን ድርሻ የተወጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዛሬው ዕለት ወደ ቴል አቪቭ አቅንተዋል፡፡