አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት አመት 14 ቢሊየን ብር የሚገመት የሃገር ሀብት ከጥፋት ማዳኑን የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በወንጀል ምርመራ ዘርፍ የ2012 በጀት ዓመት የሥራ ክንውንና በ2013 የሥራ ዕቅድ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ግምገማ አድርጓል።
ግምገማው በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ በጎ ውጤቶችን ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለማረም ያለመ መሆኑን የቢሮው ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሰለሞን ዳጨው ገልጸዋል።
በዚህም እንደ ሃገር የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በማጣራትና በመመርመር የጥፋቱን ተሳታፊዎች ለህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ጠንካራ ሥራ መሰራቱ ተገምግሟል።
በታክስና ጉምሩክ፣ በግብር ስወራ፣ በሙስና፣ በፋይናንስ ተቋማት ወንጀሎች፣ በሰዎችና በገንዘብ ዝውውር፣ በአደገኛ እፅ ማዘዋወር፣ በኮንትሮባንድና በሌሎችም የተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ማጣራቱንም ተናግረዋል።
በዚህም በአጠቃላይ ከ14 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የሃገር ሀብት ከጥፋት መታደጉንም ገልጸዋል።
በግምገማው ሕግ በማስከበር ሂደት እንደ ክፍተት የተለዩ የምርመራ መዝገቦችን ለማጠናቀቅና ዘመኑን የሚመጥን የወንጀል ምርመራ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አቅጣጫ እንደተቀመጠ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

