አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ለማረጋገጥ እያከናወነች የሚገኘው ስራና ውጤት በዓለም የምግብ ጉባኤ ላይ ለሌሎች ሀገራት በአርያነት ተነስቷል።
የዓለም ምግብ ጉባኤ ”ለተሻለ ምግብና ለተሻለች ነገ እጅ ለእጅ እንያያዝ” በሚል መሪ ሐሳብ በጣሊያን ሮም እየተካሔደ ይገኛል።
በጉባዔው የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳን (ዶ/ር) ጨምሮ የግብርና ባለሙያዎች ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ናቸው።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) 80ኛ የምስረታ ዓመት የድርጅቱን ያለፉት ዓመታት ስራዎች በሚዳስሱ እንዲሁም ቀጣይ ራዕይ በሚገልጡ ዝግጅቶች እየተከበረ ሲሆን÷ የዓለም ምግብ ጉባኤም የዚሁ አካል መሆኑ ተመላክቷል።
በጉባኤው ላይ የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳሲልቫ እና የፋኦ ዳይሬክተር ጀነራል ኪዩ ዶንግዮን እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ተመራማሪዎች ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም÷ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በሀገር በቀል እውቀትና በራስ አቅም ለመሸፈን ተግባራዊ አድርጋ በአጭር ጊዜ የተገኘው ውጤት ከራስ አልፎ ለጎረቤትና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መልካም ተሞክሮ መሆኗን አንስተዋል።
በመድረኩ ዓለም ላይ አሳሳቢ የሆነው የምግብ ፍላጎት አለመስተካከል ፈተና ሆኖ እንዳይቀጥል ሀገራት፣ ተቋማትና ግለሰቦች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ጥምረት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ጉባኤው በቀጣይ ቀናት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ተግባራዊ ውጤት ላመጡ ሀገራትና ተቋማት እውቅና እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
በፍሬህይወት ሰፊው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!