አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተሟላ ሁኔታ ውጤታማ እንዲሆን የዓለም ባንክ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትሩ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን ከባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሚ ዲዮፕ ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በግዙፍ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደትና የሁለቱን ወገኖች ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ የአለም ባንከ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙ የልማት ስራዎች እያደረገ ያለውን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዘላቂነት እንዲተገበር የዓለም ባንክ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሚ ዲዮፕ የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማድረግ ያሳየውን አመራር አድንቀው፥ ተቋማቸው የኢትዮጵያን የልማት ኢኒሼቲቮች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

