Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው – የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን ያካተተው ልዑክ ተሳትፈዋል፡፡

አቶ አህመድ በዚሁ ወቅት÷ ባንኩ ለኢትዮጵያ ልማት ላደረገው ዘለቂ እና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን በማንሳትም ሪፎርሙ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣትን ጨምሮ የተሻለ የውጪ ምንዛሪ ክምችት እንዲኖር ማድረጉን፣ የኑሮ ውድነት ማረጋጋቱንና የወጪ ንግድ ማሳደጉን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በግብርና፣ ሰው ኃይል ልማት፣ የግሉ ዘርፍ እድገት እና ቀጣናዊ ትስስርን በመሳሳሉ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ በበኩላቸው÷ ታሪካዊ ለሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መሳካት አመራር ለሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አድናቆታቸውን ገልጸው፤ ሪፎርሙ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያፋጥን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው ብሄራዊ ምክክር ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ለአካታችና ዘላቂ ልማት በር ከፋች የሆነ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ሲሉም ማረጋገጣቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል፡፡

Exit mobile version