አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የደንበኞችን ቁጥር ከ100 ሚሊየን በላይ ለማድረስ እየሰራ ነው አሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ፡፡
የተቋሙን የሦስት ዓመት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ÷ ኢትዮ ቴሌኮም እስከ ፈረንጆቹ 2028 “ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር” በሚል መሪ ሐሳብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ኢትዮ ቴሌኮም ቀደም ሲል እንደ 4ጂ፣ 5ጂ፣ ቴሌ ብር፣ ቴሌ ገበያ፣ የስማርት ሲቲ እና ስማርት ግብርና ፕሮጀክቶችን ይፋ ማድረጉን አውስተዋል፡፡
ተቋሙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ ገልጸው÷ የቴክኖሎጂ ጥራት እና ተደራሽነት ለማስፋት የአራተኛው ትውልድ (4ጂ) ኔትወርክ ተጠቃሚዎችን ወደ 99 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በአጠቃላይ የሦስት ዓመቱ ስትራቴጂ ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬት የላቀ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በትናንትናው ዕለት የሀገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለመውን “ዘ ኔክሰስ” የተሰኘ አዲስ ስትራቴጂ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በሚኪያስ አየለ