Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሊቨርፑል ከማንቼስተር ዩናይትድ …

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ8ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ማንቼስተር ዩናይትድን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

የሊጉን ዋንጫ በተመሳሳይ 20 ጊዜ ማሳካት የቻሉትን ሁለቱን ቡድኖች በሚያገናኘው ጨዋታ÷ ወቅታዊ ብቃታቸው ተመጣጣኝ ባይሆን እንኳን በየትኛውም አጋጣሚ እርስ በርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ያገኛል።

በ2024/25 የውድድር ዘመን ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ ለ20ኛ ጊዜ በማሳካት ማንቼሰተር ዩናይትድ ለብቻው ይዞት የነበረውን ክብረ ወሰን መጋራቱ ይታወሳል።

ላንክሻየር ደርቢ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ካሉ ትልልቅ ደርቢዎች መካከል አንዱ ነው።

የአምና የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ዘንድሮም ለዋንጫው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው የሊጉ ቡድኖች መካከል ይጠቀሳል።

በሊጉ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን የተሸነፈው ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ የሚጠበቅ ሲሆን÷ በውድድር ዓመቱ በሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ ድል ሲቀናው በሁለቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡

በአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ በውድድር ዓመቱ ወጥ ብቃት ለማሳየት እየተቸገረ ይገኛል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ በውድድር ዘመኑ እስካሁን ካደረጓቸው ሰባት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፈው በአንዱ አቻ ተለያይተው በሶስቱ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጉ ተከታታይ ጨዋታውን ለማሸነፍ በዛሬው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሁለቱን ሲያሸንፍ ማንቼስተር ዩናይትድ በአንዱ ድል አድርጎ በሁለቱ ጨዋታ ደግሞ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል፡፡

በሁለቱ ክለቦች ታሪክ ከፍተኛ የመሸናነፍ ውጤት የተመዘገበው በፈረንጆቹ 2023 የውድድር ዓመት ሊቨርፑል 7 ለ 0 እና በ1916 7 ለ 1 በሆነ ውጤት ማንቼስተር ዩናይትድን ያሸነፈበት እንዲሁም በፈረንጆቹ 1928 ማንቼስተር ዩናይትድ 6 ለ 1 በሆነ ውጤት ሊቨርፑልን ያሸነፈበት ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ሊቨርፑል ከ ማንቼስተር ዩናይትድ በታሪካቸው በሁሉም ወድድሮች ባደረጓቸው ጨዋታዎች ማንቼስተር ዩናይትድ 91 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን÷ ሊቨርፑል 82 ጊዜ ድል ሲቀናው 71 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በሊቨርፑል እና ማንቼስተር ዩናይትድ መካከል የሚደረገውን ተጠባቂ ጨዋታ ማይክል ኦሊቨር በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት 30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ይደረጋል፡፡

ከዚህ ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 10 ሰዓት ላይ ቶተንሃም ሆትስፐር ከ አስቶንቪላ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አስቶንቪላ ሶስቱን ሲያሸንፍ÷ ቶተንሃም ሆትስፐር በሁለቱ ድል አድርጓል።

የ8ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ነገ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ዌስትሃም ዩናይትድን ከብሬንትፎርድ በማገናኘት ይጠናቀቃል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version