አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ የኅብረተሰብ ጤና አገልግሎት እንዲሻሻል ያላት የመሪነት ሚና የሚደነቅ ነው አለ ዓለም አቀፉ የክትባቶች ጥምረት (ጋቪ)፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከዓለም አቀፉ የክትባቶች ጥምረት (ጋቪ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳኒያ ኒሽታር ጋር በጤናው ዘርፍ ትብብር ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ የተደረገው ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ሲሆን፥ ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ የጤና መሰረተ ልማትና በበሽታ መከላከል ስራዎች ላይ መክረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ስትራቴጂ በዋናነት በበሽታ መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዘርፉ የሰው ኃይል ማብቃት ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም በቅርብ ጊዜያት በተለይም ለህጻናት ክትባትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ስኬታማ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉ ሲሆን፥ ጋቪ በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ በመደገፍ ረገድ እያከናወናቸው ላሉት ተግባራት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳኒያ ኒሽታር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ያላትን አስተዋጽኦ ጨምሮ በአፍሪካ የኅብረተሰብ ጤና አገልግሎትን ለማሳደግ ያላትን የመሪነት ሚና አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ በመድሃኒት ቁጥጥር በዓለም ጤና ድርጅት 3ኛ ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ (ማቹሪቲ ሌቭል 3) በማግኘቷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ጥምረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በጤናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የጤና ስርዓቱን በዘላቂነት ማጠናከር እንዲቻል ዘርፉን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችሉ አማራጮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡