Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የተወለዱት በቀድሞ አጠራር በወሎ ክፍለ ሀገር ለጋምቦ ወረዳ፣ ገነቴ በምትባል መንደር ግንቦት 21 ቀን 1929 ዓ.ም ነው፡፡

ገና በለጋ ዕድሜያቸው የእውቀት ፍቅር በልባቸው ሠርፆ ገበሬ አባታቸውን በማስፈቀድ የእስልምናን ዕውቀት ለመቋደስ የሕይወት መንገድ መጀመራቸውን በሕይወት እያሉ በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ከ50 ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ኡስታዛቸውን (መምህራቸውን) በመፈለግ ሲሆን÷ በወቅቱ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ሊቀመንበር ከነበሩት ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ዘንድ ጀምረውት የነበረውን ትምህርት ለመቀጠል እንጂ በከተማዋ ለመኖር አልነበረም፡፡

እርሳቸው መምህራቸውን የፈለጉትን ያህል ደሴ ከተማ ውስጥ ያስተምሯቸው የነበሩ ተማሪዎች ደግሞ እርሳቸውን ፍለጋ ተከትለው መጥተዋል፡፡

ሆኖም ለዓመታት የሰበሰቡት እውቀት ሌሎችን ለማስተማር ከበቂ በላይ መሆኑን ሐጂ ሣኒ ስለተረዱ በአንዋር መስጂድና በመስጂድ ኑር እንዲያስተምሩ ተመደቡ።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ግማሽ ቀኑን ለራሳቸው እውቀትን ሲሰበስቡ ቀሪውን የቀን እኩሌታና ምሽት ላይ በማስተማር ያሳልፉ ነበር፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከማስተማር ባሻገር ከ50 በላይ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን ጽፈዋል፤ ቅዱስ ቁርዓንን ተርጉመዋል፤ የቁርዓን ትርጉም ሥራቸውም በሲዲ ተሠራጭቷል፡፡

ከ50 ዓመታት በላይ በዘለቀ የአዲስ አበባ ቆይታ ቅዱስ ቁርዓንን ከ300 ጊዜ በላይ በትርጉም ያስተማሩ ሲሆን÷ ከጻፏቸው መጻሕፍት የሕትመት ብርሃንን ያገኘው አንድ ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ሃይማኖታዊ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የሚጠሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ፤ በ1967 ዓ.ም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ሲመሰረት የምክር ቤቱ አባልና የዑለማ ሊቀመንበር ነበሩ፡፡

ከ2010 መጋቢት እስከ ግንቦት ወር 2014 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በአንድ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክታቸው÷ “ሰው ሁኑ፤ ሰውነት ይቀድማል” በሚለው ምክራቸው እና ተግሳጻቸው በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚወሱ አባትም ናቸው።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በተለያዩ ጊዜያት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ባደረባቸው ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ትናንት ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን÷ ሥርዓተ ቀብራቸው በዛሬው ዕለት እንደሚከናወን ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version