Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክት ÷ ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ አረጋውያን፣ አፈ ማር ከሆኑ መካሪዎችዋ መካከል አንዱ የሆኑትንና ለመወደድ የታደሉትን የዘመናችን ጌጥ አጥታለች ብለዋል፡፡

እግዚአብሔር በየዘመናቱ ሀገርን ያለ መካሪ፣ ሕዝብን ያለዘካሪ አይተወውም ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ÷ ለዚህም ምስክሩ ታላቅ አረጋዊ፣ የበሳል አእምሮ ባለቤት፣ ሀገርን የሚወዱ፣ ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ የተጠቁት ወዳጅ፣ የትውልድ አባት የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ነበሩ ነው ያሉት፡፡

ይህንን የድካም ዓለም መገላገል ለእርሳቸው ዕረፍት ቢሆንም ለሀገር ግን ታላቅ ጉዳት ከመሆኑም በላይ ዕድሜን ከጥበብ ጋር ያዋሐዱ በሁሉ ዘመን አይገኙምና ሐዘናችን ጥልቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

Exit mobile version