Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ እና ኳታር የኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኳታር የኢንቨስትመንት እና የልማት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ከኳታር አቻቸው አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ እና ከኳታር የልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፋሃድ ሃማድ አል ሱለይቲ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል በመሠረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በልማት ስራዎች ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለመፍጠርና ያላቸውን ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት እድል በማስረዳት፥ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን አጋርነት ከፍ ባለ ደረጃ ትመለከታለች ያሉት ሚኒስትሩ፥የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት ያደነቁት የኳታር የገንዘብ ሚኒስትር አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ በበኩላቸው፥ በንግድና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅም መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ጠንካራ ፍላጎት እንዳላትም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

የኳታር የልማት ፈንድ አካታች እድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ፋሃድ ሃማድ አል ሱለይቲ ናቸው።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና በኳታር መካከል ጥልቅና የረጅም ጊዜ ትብብር ለመፍጠርና ጠንካራ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመለየት እንዲቻል የጋራ የቴክኒክ ቡድን ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version